በመዲናዋ ባለፉት ሥድስት ወራት ከ195 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጠረ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ባለፉት ሥድስት ወራት ከ195 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጠረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ለ195 ሺህ 112 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።
ከንቲባ አዳነች በጉባዔው ላይ የከተማ አሥተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ፤ ለ195 ሺህ 112 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
ለዚህም የሥራ ስምሪት ዘርፎችን ማስፋት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ገልጸው፤ የከተማ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ እና በቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ከ250 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አመላክተዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በፍትሐዊነት ማሳተፉን ጠቅሰው፤ በዚህም መሠረት 53 በመቶ ሴቶች፣ 49 በመቶ ወጣቶች እንዲሁም 6 ነጥብ 8 በመቶ አዲስ ተመራቂዎች ናቸው ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ የዜጎችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸው ሥራዎች ውጤት እያመጡ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።