የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጡ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጡ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ የመርሐ ግብሮቹ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡
በመርሃ-ግብሩ የተሳተፉ ዜጎች ከሸማችነት ወደ አምራችነት በመሸጋገር የራሳቸውን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።
በረጋሳ ጉሩሙና ኤርሚያስ ረጋሳ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ውስጥ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት በኃይሉ ኃይለማርያም እንደተናገሩት፤ በሌማት ትሩፋት አማካኝነት የሚመረተው ምርት በገበያ ላይ ያለውን የዋጋ ንረት በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በዚህም በርካታ የምርት ዓይነቶችን በማምረት ከራሳቸው አልፈው በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተቀናጀ የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር እያለማ የሚገኘው ሃይማኖት ጥላሁን፣ መንግሥት የሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል ለውጥ እንዲያመጡ እንዳስቻላቸው ገልጿል።
የራሳችንን የምግብ ዋስትና ከመሸፈን ባለፈ ለሌሎች ዜጎች ምርታችንን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረብን ነው ሲልም ተናግሯል።
በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና መርሃ-ግብር ውስጥ የታቀፉ ዜጎች ስራው አዲስ የኑሮ ተስፋና ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድል ይዞላቸው መምጣቱን ገልጸዋል።
በረጋሳ ጉሩሙና ኤርሚያስ ረጋሳ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ውስጥ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ወልደጻድቅ ዳምጤ፤ መርሃ-ግብሩ ከገቢ ምንጭነት ባለፈ ታታሪነትንና አዲስ የሥራ ባህልን በማስረፅ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ብሏል።
በተመሳሳይ በሰገነት የተቀናጀ የከተማ ግብርና ውስጥ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ዘነበ ጣሴ በበኩሉ፤ አሁን የሚያገኘው ገቢ የተሻለ በመሆኑ ራሱንና ቤተሰቡን በበቂ ሁኔታ ለማስተዳደር መቻሉን አረጋግጧል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ እንደገለጹት፤ መርሃ-ግብሩ የዕለት ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት እየሆነ ነው።
አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ባላቸው ጠባብ ቦታ አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት፣ የዶሮና የእንስሳት እርባታን በማስፋፋት የራሳቸውን ፍላጎት ከመሸፈን አልፈው ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ በተግባር ተከናውኖ፣ ዜጎች በአነስተኛ ቦታ ላይ ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ማሳያ ሆኗል።
ይህ ንቅናቄ የከተማዋን የምግብ ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈንና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው ጥረት ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።