ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ኩባንያዎች ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፍጠር አስተማማኝ አጋር ናት

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ኩባንያዎች ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፍጠር አስተማማኝ አጋር መሆኗን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ገለጹ፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር፤ ህብረቱ ከአውሮፓ የንግድ ምክር ቤት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የንግድ ምህዳሩ እየሰፋ በመምጣቱ 180 የሚጠጉ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የአውሮፓ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ትስስራቸውን ለማሳለጥ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ሚያዚያ ወር የአውሮፓ ህብረትና የኢትዮጵያ ንግድ ፎረም ይካሄዳል ብለዋል፡፡

ፎረሙ ኢትዮጵያ ያሏትን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለማስተዋወቅ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሯ፤ ሪፎርሙ ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት በርካታ የአውሮፓ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲቀላቀሉ አድርጓል ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የመቀላቀል ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን በማንሳት፤ ለሪፎርሙ ስኬት በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በታዳሽ ኃይል፣ ግብርና፣ ጤናና ሌሎች የትብብር መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በቀጣይም ህብረቱ በሰርኩላር ኢኮኖሚ፣ ከተማ ልማትና ሌሎች የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም