ለመገንባት ከታቀዱ 100 ሺህ ቤቶች 97 ሺህ ቤቶች ወደ ግንባታ ሂደት ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለመገንባት ከታቀዱ 100 ሺህ ቤቶች 97 ሺህ ቤቶች ወደ ግንባታ ሂደት ገብተዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- በመንግስትና የግል አጋርነት እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ በጀት ለመገንባት ከታቀዱ 100 ሺህ ቤቶች 97 ሺህ ቤቶች ወደ ግንባታ ሂደት መግባታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሔደ ነው፡፡
በጉባኤው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ለከተማው ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡
የቤት ልማት አፈጻጸምን በተመለከተ ከንቲባዋ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ባለፉት ስድስት ወራት በመንግስት በጀት እና በበጎ አድራጎት 12ሺህ 257 የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ለልማት ተነሺዎችና ለሀገር ባለውለታዎች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።
በቤት ልማት አቅርቦት ላይ በተሰራው ስራ በመንግስት በጀትና በበጎ አድራጎት 11ሺህ 550 የመኖሪያ ቤቶችና 707 የንግድ ቤቶች መተላለፋቸውን ነው የገለፁት።
በበጎፈቃድ ከለውጡ በኃላ 45 ሺህ 566 ቤቶች የተገነቡ ሲሆን በዚህ ስድስት ወራት ብቻ 4 ሺህ 990 ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
በመንግስትና የግል አጋርነት እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ በጀት ለመገንባት ከታቀዱ 100 ሺህ ቤቶች 97 ሺህ ቤቶች ወደ ግንባታ ሂደት የገቡ ሲሆን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በ65 የህብረት ስራ ማህበራት ለተደራጁ 5 ሺህ 110 የቤት ገንቢዎች ጠንካራ ድጋፍ በመደረጉ 42 ማህበራት ወደግንባታ ምዕራፍ መሸጋገራቸውንም ነው ያብራሩት።
በግልና በሪልስቴት 13 ሺህ 517 ቤቶች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን በኮሪደር የለሙ 810 የንግድ ቤቶች በልማት ለተነሱ አነስተኛ ነጋዴዎች ለማስተላለፍ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።