ቀጥታ፡

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶአደሮች ለበልግ አዝመራው በኩታ ገጠም ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል

ጭሮ ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶአደሮች ለበልግ አዝመራው በኩታ ገጠም ተደራጅተው ወደ እርሻ ሥራ መግባታቸውን ተናገሩ። 

አርሶ አደሮቹ ለበልግ አዝመራው ማሳን በተገቢው መንገድ በማዘጋጀት የተሻለ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዞኑ በጡሎ ወረዳ ገመቺስ ቀበሌ አርሶአደር ታደሰ ዳዲ በሰጡት አስተያየት ከሌሎች አርሶአደሮች ጋር በቡድን ስራ በአራት ጥማድ ማሳቸው ላይ ለዘር ዝግጅት ጀምረዋል።


 

በልማቱ የግብርና ባለሙያዎች በማሳ አዘገጃጀትና በግብዓት አጠቃቀም ዙሪያ የሙያ እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

ከሌሎች አርሶአደሮች ጋር በኩታ ገጠም ተደራጅተው ሁለት ሄክታር ማሳ በትራክተር እያረሱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አርሶአደር አህመድ አሊዪ ናቸው።


 

በወቅቱ ከበቆሎ በተጨማሪ ቦሎቄ እና ድንች በማልማት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ እቅደው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የጡሎ ወረዳ ግብርና ባለሙያ አቶ ሳኒ አብደላ እንደገለጹት፤የዞኑ አርሶአደሮች በበልግ አዝመራው ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።


 

መሬት አርሰው ከማዘጋጀት በተጨማሪ በግብአት አጠቃቀም እና በሰብል እንክብካቤ በቅርበት ድጋፍና እገዛ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

በዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ መደቅሳ ዴሬሳ እንደገለፁት፤ በዞኑ 15 ወረዳዎች የማሳ ዝግጅት ስራ እየተካሄደ ነው።

በዞኑ በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ67 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በበልግ አዝመራ ለማልማት መታቀዱንና ከዚህም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በወቅቱ በአብዛኛው የአገዳ እና ብርዕ ሰብሎች እንደሚለሙ ገልፀው አርሶአደሮቹ መሬትን በወቅቱ እንዲያዘጋጁና ግብአቶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ስራ መጠናከሩን ገልጸዋል።

እስካሁንም ለበልግ አዝመራው የሚውል ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ አርሶአደሩ ጋር መድረሱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም