ቀጥታ፡

በጠቅላላ ምርጫው የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲጎለብት የድርሻችንን እንወጣለን - የምክር ቤት አባላት

ወልቂጤ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- በጠቅላላ ምርጫው የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲጎለብትና ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለፁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ፣ አካታች እና ካለፈው ምርጫ የተሻለ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

ጠቅላላ ምርጫውን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላትም በምርጫው የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲጎለብትና ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

ከምክርቤቱ አባላት መካከል አቶ ሰላሙ ሱላሞ እንደገለፁት፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ማሳካት የሚቻለው የህግ የበላይነትን በማክበር፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ መሳተፍ እና መተግበር ሲቻል ነው። 


 

በመሆኑም ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ምርጫ እንዲከናወን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አብራርተዋል ።

መራጩም የመምረጥ መብቱን ተጠቅሞ ይበጀኛል ያለውን ፖርቲ እንዲመርጥ በማስተማር ባገኙት አጋጣሚ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል ተፈራ ሞላ (ዶ/ር) ጠቅላላ ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ባገኙት አጋጣሚ ለህዝቡ እያስገነዘቡ መሆኑን አስታውሰው ፤ ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። 


 

ምርጫው ሰላማዊና ተአማኒነት ያለው ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ፓርቲዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች የሚጠበቅባቸውን ግዴታና ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚያከናውኑም አስረድተዋል።

ምርጫው ለዴሞክራሲ፣ ለዘላቂ ሰላምና ለልማት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ  የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አሰለፈች ሃይሌ ናቸው።


 

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም