ቀጥታ፡

ስድስተኛው ሀገር አቀፍ የሠላም ኮንፍረንስ በሆሳዕና ከተማ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-ስድስተኛው ሀገር አቀፍ የሠላም ኮንፍረንስ  "ሃይማኖቶች ለሠላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ  በሆሳዕና ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት የሠላም ኮንፍረንሱ  የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ህዝባዊ የሠላም ኮንፍረንሱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ኮንፍረንሱን አስመልክተው እንደገለጹት፣ ሠላም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ለህዝቦች አብሮነት መሰረታዊ ዋልታ ነው። 

ኮንፍረንሱ በኢትዮጵያ ሠላምን ለማጽናት፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በሠላም ግንባታ ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ እና በዜጎች መካከል ይበልጥ አብሮነት እና መቀራረብን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀገር እድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም ዜጋ ለሠላም ግንባታ በቁርጠኝነት ሲቆም መሆኑን ጠቁመው፣ በሆሳዕና ከተማ የሚካሄደው ይህ ኮንፍረንስ ይህንን እውነት ለማጽናት ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በተካሄዱት ኮንፍረንሶች በሠላም ግንባታ ረገድ አዎንታዊ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም