በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለትውልድ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለትውልድ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች የተማሪዎችን ውጤት ከማሻሻል ባለፈ ለትውልድ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ መክፈታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሔደ ነው፡፡
በጉባኤው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ለከተማው ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡
የትምህርት ዘርፍ አፈጻጸምን በተመለከተ ከንቲባዋ ባቀረቡት ማብራሪያ፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ዘርፉ በሥነ-ምግባር የታነጸና ውጤታማ ትውልድ የሚፈራበት፣ እንዲሁም ብቁና ተወዳዳሪ መምህራን የሚገኙበት እንዲሆን ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት በየዓመቱ እያሳየ የመጣው እድገት የተከናወኑ ተግባራት ፍሬ እያፈሩ መሆናቸውን ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ መልኩም በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል የነበረውን የተማሪዎች ውጤት ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ማቀራረብ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የፈጠረው ትልቅ ዕድል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች የአብሮነት፣ የአንድነትና የመቻቻል እሴቶች ማጎልበቻ እንዲሆኑ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በአገሩ ጉዳይ የማይደራደርና ለብሔራዊ አንድነት የሚሠራ ትውልድ ለመፍጠር፣ ለአገራዊ ብልጽግና ስኬት የማይተካ ሚና ያለው ዜጋ ለማፍራት እንዲሁም እንደ አገር ለተጀመረው የትውልድ ግንባታ ሂደት ጉልህ አስተዋጽኦ ለማበርከት አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል በ“ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ በርካታ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተሰሩ ስራዎች የትምህርት ጥራትን ከማሻሻል አንጻር ጉልህ ሚና መጫወቱንም ተናግረዋል፡፡