ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚሁ ወቅትም፤ ምክር ቤቱ የ3ኛ ዙር የአዲስ አበባ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ቃለ-ጉባዔ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ግዢና ንብረት አሥተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ የዳኞች ሹመት ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።


 

በአሁኑ ወቅትም የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤት በማቅረብ ላይ ናቸው።

በሪፖርታቸውም፤ ከለውጡ ወዲህ ግልጽ ከሆነ የብልጽግና እሳቤ በተቀዱ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች እየተመራች የምትገኘው አዲስ አበባ በርካታ ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኗን ጠቅሰዋል።

በዚህም በተከናወኑ በርካታ ተግባራት በዘመናት መካከል የተመላለስንበትን የኋላ ቀርነትና የድህነት ታሪክ እንዲሁም ጎስቋላ ገጽታን እየፋቅን፣ ከመጥፎ ጠረን እየራቅን፣ ከድንግዝግዙ እየተላቀቅን አሁን ወደምንገኝበት የተጨበጠና ወደሚታይ ብርሃናማ ምዕራፍ ተሸጋግረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም