ቀጥታ፡

ማህበሩ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ራሳቸውን እንዲችሉ እያገዘ ነው

ባህርዳር ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-የአማራ ሴቶች ማህበር በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን በገቢ ማስገኛ ስራዎች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

ማህበሩ የግማሽ ዓመት የተግባር ዕቅድ አፈፃፀሙን  በባህር ዳር ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።

‎‎የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ገነት ወንድም እንደገለፁት ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 288 ሴቶችን በተለያዩ የሙያ መስኮች በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን አብራርተዋል።

ማህበሩ ከራሱና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር‎ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር መድቦ ማሰራጨቱንም አመልክተዋል።

ማህበሩ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙ ሴቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ባለፈ ፆታዊ ጥቃትንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።


 

‎‎የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዝና ጌታቸው በበኩላቸው፣ ማህበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

‎ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ሥራዎች እንዲያጠናክር ጠይቀው፣ ቢሮው ለዚህ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

‎‎‎በመድረኩም የማህበሩ የክልልና የዞን አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም