ቀጥታ፡

የዳራሮ በዓልን እሴቱን ጠብቆ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል 

ዲላ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-የጌዴኦ ዘመን መለወጫ ''ዳራሮ'' በዓል እሴቱ ተጠብቆ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል በተደረገ ጥረት ውጤት መገኘቱን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

የዳራሮ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫና የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በዲላ ከተማ ተካሄዷል።


 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) የጎዳና ላይ ሩጫው ጤናችንን እየጠበቅን የዳራሮ በዓልን ማስተዋወቅን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

የአንድነትና የምስጋና በዓል የሆነው ''ዳራሮ'' በዞኑና ከዞኑ ውጭ በአዲስ አበባና በውጭ ሀገር እየተከበረ መሆኑን አንስተው ነገ በዲላ ከተማ የማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ይከናወናል ብለዋል።


 

በዚህም የበዓሉን እሴቶች በመጠበቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማሸጋገር ባለፈ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል በተደረገ ጥረት ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስፖርት ከበሽታ ራስን ከመጠበቅ ባለፈ ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።


 

የዳራሮ የሰላም፣ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቹን በዘላቂነት ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

መርሃ ግብሩ ጤናን ከመጠበቅ በተጓዳኝ ዳራሮን በጋራ ለማክበር ያስቻለ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የስፖርት እንቅስቃሴው ተሳታፊ ወይዘሮ  ምስጋና በቀለ ናቸው።


 

ስፖርት የአንድነትና የፍቅር መሰረት መሆኑን አንስተው ይህም ከዳራሮ በዓል ጋር መተሳሰሩ የበዓሉን ባህላዊ ይዘቶች ለማጉላት የሚያስችል ነው ብለዋል።

አትሌት ሎሚነሽ አሰፋ በበኩሏ በውድድሩ በሴቶች ዘርፍ ሶስተኛ መውጣቷን አንስታ የወድድሩ ደማቅ ድባብ ትልቅ ሞራልና ደስታን የሚፈጥር ነው ብላለች።እሷን ለመሰሉ አትሌቶችም የውድድር እድልን የፈጠረ መሆኑን ነው ያነሳችው።


 

የጌዴኦ ዘመን መለወጫ ''ዳራሮ'' በዓል ዛሬ እና ነገ በተለያዩ ትዕይንቶች በመታጀብ በዲላ ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም