ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን እያደረግን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን እያደረጉ መሆናቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ልምዶች በተሻለ መልኩ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና አካታች እንዲሆን መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው መራጮች ለምርጫው እንደ ጡብ፣ ተሳታፊ ፓርቲዎች ደግሞ እንደ ማገር ናቸው በሚል የገለጹ ሲሆን፤ የምርጫ አውዱን ለማስፋት ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ ለምርጫው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡


 

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፕሬዝዳንትና የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት የምርጫና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አላምረው ይርዳው፤ ምርጫ የሕዝብ ሉዓላዊ ድምፅ የሚሰማበትና የሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት ትልቅ መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጥምረታቸው በአሁኑ ወቅት በበርካታ ክልሎች የዕጩዎች ምልመላና ምዝገባ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የድርጅታዊ መዋቅርን የማጠናከርና የምርጫ ማኒፌስቶን የማዘጋጀት ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው የድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።


 

በተመሳሳይ የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበርና የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ዋና አስፈጻሚ አቶ ዳሮት ጉምአ፤ ለዘንድሮው ምርጫ የሚመጥን ዝግጅት መጀመራቸውን አረጋግጠዋል።

ምርጫው ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ እንዲሆን ከምርጫ ቦርድ ጋር በቅርበት እየሠሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳሮት፤ ፓርቲያቸው በምርጫው ለመፎካከር የሚያስችሉ ስልቶችን ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።

በተለይም ከአባላትና ከደጋፊዎች ጋር ተከታታይ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ በምርጫ ዝግጅትና ሂደት ላይ የጋራ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም