በሐረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሀረር፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡-በሐረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
በሐረሪ ክልል የመንግስትና የፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀመረ።
በግምገማ መድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት፤ በግማሽ በጀት ዓመቱ በክልሉ አበረታች ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።
መድረኩም ትኩረት የሚያደርገው እቅድን መሰረት ያደረገ የመንግስትና የፓርቲ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸምን በመገምገም ለቀጣይ ስራዎች ራስን ማዘጋጀት እንደሆነም አክለዋል።
የግምገማ መድረኩም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስፋት፣ የተስተዋሉ ውስንነቶችን በመሙላት የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስፋት ግብዓት የሚሰበሰብበት እንዲሁም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት የሚደረግበትና ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የፖለቲካና የአደረጃጀት ስራዎችን በአግባቡ ምልከታ በማድረግ የጋራ ግንዛቤና አረዳድ ሊኖር እንደሚገባም አክለዋል።
የመንግስት ትልቁ ስራ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ማሻሻል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይም በክልሉ ገጠር እና ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማሻሻል አንጻር የተከናወኑ ስራዎችን መፈተሽ ይገባል ብለዋል።
በዚህም ምርትና ምርታማነትን ከማጎልበት፣ የስራ እድልን ከማስፋት፣ የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ፣ ኢንቨስትመንትን ከማበረታታትና ከሌሎች አንጻር የተከናወኑ ስራዎች ይገመገማሉ ብለዋል።
የትምህርት ተሳትፎና ጥራት፣ ከጤና አገልግሎት እና ከሌሎች ማህበራዊ ዘርፍ እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ከማዘጋጃ ቤትና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አንጻር የተከናወኑ ስራዎችም በጥልቀት ይታያሉ ብለዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመቅረፍና ብልሹ አሰራሮችን ከማስወገድ አኳያም የተከናወኑ ስራዎች በመድረኩ እንደሚገመገሙ ነው ያነሱት።
በክልሉ ሰላምን ለማጽናትና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንጻር እየተከናወኑ የሚገኙትን ተግባራት ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል ።
በግምገማ መድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም፣ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳን ጨምሮ የክልሉ የመንግስትና የፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።