በዞኑ ከ379 ሚሊዮን በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች ለተከላ እየተዘጋጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ379 ሚሊዮን በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች ለተከላ እየተዘጋጁ ነው
ጊምቢ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ379 ሚሊዮን በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች ለተከላ እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት የቡናና ሻይ ልማት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም መስፍን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በዞኑ ከጅማ ግብርና ምርምር ማእከል የተገኙና በአጭር ጊዜ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞች እየተዘጋጁ ነው።
በመጪው ክረምት ለተከላ እየተዘጋጁ ያሉት የቡና ችግኞች ከ379 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውን ጠቁመው ችግኞቹ በግልና በመንግስት ጣቢያዎች እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በዝግጅቱም ከ59 ሺህ በላይ ቡና አምራች አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ለመጪው ክረምት ለተከላ እየተዘጋጁ ያሉት የቡና ችግኞችም ከ64ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚሸፍኑም አብራርተዋል፡፡
የቡና ችግኞቹ በሽታን በመቋቋም በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ለምርት የሚደርሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዞኑ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮች ያረጁ የቡና ተክሎችን እንዲጎነድሉና ነቅለው በተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች እንዲተኩ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የችግኝ ተከላው ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሐምሌ 2018 ድረስ እንደሚካሄድና አርሶ አደሮቹ ከወዲሁ የጉድጓድ ቁፋሮ መጀመራቸውን አመላክተዋል።
ለመጪው ክረምት ተከላ ከ2 ሺህ በላይ በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞችን እያፈሉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጊምቢ ወረዳ አርሶ አደር ወንድሙ ገለታ ናቸው ፡፡
መንግሥት በየዓመቱ ዝርያቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ማቅረቡ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የሆማ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አብዳታ ሊካሳ በበኩላቸው፤ ቡናን በቋሚነት በማልማት ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ጠቁመዋል።
ለመጪው ክረምት ከ3 ሺህ በላይ የቡና ችግኞችን በግላቸው እያፈሉ መሆኑን ጠቁመው፤ ከወዲሁ የጉድጓድ ቁፋሮና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት መሸፈኑ ተመላክቷል።