ቀጥታ፡

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦‎  የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ዛሬ በሊድስ ዩናይትድ እና ኖቲንግሃም ፎረስት መካከል ይካሄዳል።

ጨዋታው ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በኢላንድ ሮድ ስታዲየም ይደረጋል።

ሊድስ ዩናይትድ በ26 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ 26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።




ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ11ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 10 ጨዋታዎች ሊድስ ዩናይትድ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ኖቲንግሃም ፎረስት በአራቱ አሸንፏል። በሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታዎቹ ላይ ሊድስ ዩናይትድ 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት 17 ጎሎችን አስቆጥሯል።

ክለቦቹ ዘንድሮ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኖቲንግሃም ፎረስት 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።



ሊድስ ዩናይትድ ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። በ24ኛ ሳምንት በሊጉ መሪ አርሰናል 4 ለ 0 መሸነፉ አይዘነጋም ።

በ24ኛ ሳምንት ከክሪስታል ፓላስ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ኖቲንግሃም ፎረስት ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።

ሶስት ነጥብ ለሁለቱም ቡድኖች ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለመራቅ ወሳኝ ነው።

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም