የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት አርባምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች በአራቱ ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በዘጠኙ ሲሸነፍ በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ11 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በ18 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ድሬዳዋ ከተማ በ23 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።
በ18ኛ ሳምንት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 በማሸነፍ የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።
ድሬዳዋ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በሌላ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 18 ጨዋታዎች አድርጎ አምስት ጊዜ ድል ሲቀናው በስምንቱ ተሸንፏል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 15 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 20 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡናማዎቹ በ20 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ብቻ ያሸነፈው ወላይታ ድቻ በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል።
በ18ቱ ጨዋታዎች 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 20 ጎሎችን አስተናግዷል። ወላይታ ድቻ በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት አራት ጨዋታዎች፣ ወላይታ ድቻ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ድል አልቀናቸውም።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ይጠናቀቃል።