ቀጥታ፡

ልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን አምርቷል

አዳማ፤ ጥር 29/2018 (ኢዜአ)፡- የአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ማዳኑን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ማክሰኞ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።


 

ኢንዱስትሪዎች በተኪ ምርት፣ በወጪ ንግድና በኢኪኖሚ ድርሻ ከፍተኛ መነቃቃትና የምርታማነት እመርታ እያሳዩ እንደሆነም አመልክተዋል።


 

የአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጉልላት አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት ተኪ ምርት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ባለው ሥራ ተጨባጭ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን አብራርተዋል።

በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ለተኪ ምርት በሰጡት ትኩረት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች መመረታቸውንና በዚህም የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉንም አስታውቀዋል።

በኢኮኖሚ ዞኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ተኪ ምርቶች እየተመረቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የሕንጻና የብረት ቀለም፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ የመብራት ቆጣሪ፣ የሕጻናት ንጽህና መጠበቂያ (ዳይፐር) ይገኙበታል ብለዋል።

በአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል የቻይናው አንቴክስ ቴክስታይል ኦፕሬሽናል ማናጀር ሙክታር ከድር፤ ኩባንያው የተለያዩ አልባሳትን በማምረት ለአውሮፓ ገበያ እያቀረበና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገኙ 19ኙም ሼዶች በውጭና በሀገር ውሰጥ ባለሀብቶች የተያዙ ሲሆን፤ ከ9 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውም ተመላክቷል።

#Ethiopian_News_Agency  #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም