ቀጥታ፡

ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል የአወያይ ስልጠና በሚቀጥሉት ሳምንታት ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል የአጀንዳ ቀረፃ ማካሄድና የአወያይ ስልጠና በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ገለጹ።

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራሮች በሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ በመወያየት ክልላዊና ሀገራዊ አጀንዳዎቻቸውን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች አስረክበዋል።


 

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ፤ በአራት ዓመታት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የተከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ምዕራፎችን ገለፃ አድርገዋል።

በሂደቱም የአማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ መካሄዱን ገልጸዋል።

ከውይይቱ በተጓዳኝ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራር አባላት በጋራ ሆነው ያቀረቧቸው አጀንዳዎች የኮሚሽኑን አሳታፊነትና አካታችነት በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝነት እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በትግራይ ክልል ለሚገኙ ወገኖች ተመሳሳይ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ምክክር ማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአጀንዳ ቀረፃ በማከናወንና በሚቀጥሉት ሳምንታት የአወያይ ስልጠናን በማስጀመር ለዋናው ሀገራዊ ጉባኤ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራር አባላት ለኮሚሽኑ ያቀረቧቸው አጀንዳዎች ከዚህ ቀደም ሲደረጉ የቆዩ ጥረቶች ውጤት ነው ብለዋል።

በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች ለኮሚሽኑ ያቀረቡት አጀንዳ ቀሪ በጫካ ለሚገኙ ታጣቂዎች ትምህርት እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ምክትል ሊቀመንበርና ወታደራዊ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ፥ ለትጥቅ ትግል መነሻ የነበሩ አጀንዳዎችን በመሰነድ ለኮሚሽኑ አስረክብናል ብለዋል።


 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእስካሁኑ ክንውኖች ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችሉ በመሆናቸው ቀሪ በጫካ የሚገኙ  የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የውጭ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፥ ለትጥቅ ትግል መነሻ የነበሩ ጉዳዮችን ከኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ ጋር በማጤን የሰላም አማራጭን እንደተከተሉ ገልጸዋል።


 

በዚህም የተሳሳተ ትርክት፣ የሕገመንግስትና ተያያዥ ጉዳዮች የተካተቱባቸውን አጀንዳዎች በማደራጀት በጋራ የምክክር መድረክ መግባባትን መፍጠር የሚስችሉ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ እንዳስረከቡ ተናግረዋል።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ እያሱ አባተ፥ በሰላም ስምምነቱ መነሻነት እንዲፈቱ የሚፈልጓቸውን የተቆጠሩ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በሰላማዊ አማራጭ ለህዝብ ተጠቃሚነትና ለኢትዮጵያ ህልውና በሚበጁ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

በርክክብ ሥነስርዓቱ ማጠቃለያ ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ የድርጅቱ አመራር አባላት በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለመሳተፍ ለወሰዱት ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም