ቀጥታ፡

ማዕከሉ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ይደርስ የነበረውን መጉላላት አስቀርቷል

ባህር ዳር፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ ባህርዳር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ቀደም ሲል ይደርስ የነበረውን መጉላላት እንዳስቀረላቸው ተገልጋዮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜ ከመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራርያ፣ አገልግሎቱ የተጀመረበት ጊዜ አጭር ቢሆንም በዘርፉ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለና በቀጣይም የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት  በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።


 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር ቀደም ሲል ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል።

ከማዕከሉ ተገልጋዮች መካከል አንዷለም ሞላ አንዱ ነው። እርሱ እንደሚለው፣ቀደም ሲል የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ክፍለ ከተማና ቀበሌ ሲሄድ ጉዳዩ ሳይፈጸም ተደጋጋሚ ቀጠሮ ብቻ ይሰጠው ነበር።


 

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር የሚፈልገውን አገልግሎት በፍጥነት ማግኘት እንዳስቻለው ገልጿል።።

ሌላው የማዕከሉ ተገልጋይ አታለል ሙሴ በአንድ ቦታ ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ አገልግሎቶችን በማግኘቱ ጊዜውንና ወጪውን እንደቆጠበለት ተናግሯል።


 

አገልግሎቱ ቀደም ሲል ሲነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በመፍታት ለተገልጋዩ እፎይታ የሰጠ መሆኑንም አመልክቷል።

በማዕከሉ የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላዋ ተጋልጋይ አለሚቱ ንጉሴ ናቸው።


 

እንዲህ አይነት አገልግሎቶች መጉላላትን በመቀነስ የህዝብን እርካታ የሚጨምሩ በመሆናቸው በሁሉም አካባቢዎች ሊሰፉ ይገባልም ብለዋል።

የባህር ዳር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ ማስረሻ ፈንታ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ የ12 ተቋማት 65 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ታግዘው እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕከሉ እየተሰጡ ከሚገኙ አገልግሎቶች መካከል  የባንክ፣ የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የትራንስፖርት፣ የመሬት ጉዳዮች፣ የንግድና የውሃና ፍሳሽ ይገኙበታል ብለዋል።


 

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት መምሪያ ሃላፊ ጤናው ምህረቱ፤ ቀደም ሲል ሕብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ  በርካታ ቅሬታዎች ሲያነሳ እንደነበር አስታውሰዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በፍጥነትና በጥራት መስጠት መጀመሩ የተገልጋዮችን እንግልት በማስቀረት ቅሬታውን ፈቷል ብለዋል።


 

ማዕከሉ አሁን ለይ በቀን 325 ያህል ተገልጋዮችን እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እተደረገ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም