የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሊያሸጋግር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሊያሸጋግር ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሊያሸጋግር መሆኑን አስታወቀ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ጋር አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ጋር ተፈራርመዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ተቋማትን ወደ ዘመናዊ አሰራር ለማሸጋገር ጉዞ ጀምራለች።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴርም አሰራሩን ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው ስምምነትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ የልማት ስራዎች በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆናቸውን በዘመናዊ አሰራር ለመከታተል እና ለማረጋገጥ የዲጂታል ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።
የልማት አስተዳደር ስራዎችና ፖሊሲዎች የሚያመጡትን ውጤት በትክክለኛ መረጃ ተመስርቶ ግምገማ ለማድረግ ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የጥቅል አገራዊ ምርት ዕድገት እና ጥራትን ለመመዘንም ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መረጃን ተንትኖ ስራ ላይ ማዋል ዘመናዊ መሰረተ ልማት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሰል ስራ ላይ የተሰማራው ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ስራው እንዲሳለጥ ፕሮጀክቱን ከተቀመጠው ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
ለዚህም የሁለቱም ተቋማት የቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።