መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ እየመለሰ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ እየመለሰ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
ሻኪሶ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ድጋፍ የሚገነባው የሻኪሶ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት የግንባታ ስራ ተጀምሯል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት መንግስት የህዝብን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የግንባታ ስራው የተጀመረው የሻኪሶ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክትም አካባቢው በቡና፣ በማዕድናትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በማልማት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሚሰራቸው ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው መገንባት የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካባቢውን ለማልማት ላደረገው ዕገዛ ያመሰገኑት አቶ ሽመልስ፤ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ አዲስ አበባን ከሀገር ውስጥ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ በርካታ በረራዎች እንዳሉት ጠቁመዋል።
የሻኪሶ አውሮፕላን ማረፊያም ተጨማሪ የአየር መንገዱ መዳረሻ በማድረግ የጉጂ ዞን የተፈጥሮ ሀብትን ለማልማት ተደማሪ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀመር የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የራሱ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በስፍራው የአውሮፕላን መንደርደሪያ እንደነበር አስታውሰው የክልሉ መንግስት የአውሮፕላን መንደርደሪያውን ወደ ንግድ አውሮፕላን ማረፊያነት ለመቀየር ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ግንባታውን ማስጀመሩን ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ በተያዘለት ጊዜ አገልግሎት እንዲጀምርም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
የሻኪሶ አውሮፕላን ማረፊያ በ124 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በይፋዊ የግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልልና የጉጂ ዞን አመራሮች እንዲሁም አባገዳዎች ተገኝተዋል፡፡