ቀጥታ፡

በቡና ዘርፍ የተከናወኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ በቡና ዘርፍ የተከናወኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከምስራቅ አፍሪካ ፋይን ኮፊ ማህበር (AFCA) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 22ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ (Africa Fine Coffee) ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም በጀመረው በዚህ መድረክ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ዓለም አቀፍ እንግዶች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 469ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ገልጸዋል፡፡

ይህ ውጤት በሀገሪቱ የቡና ታሪክ ከፍተኛው የገቢና የጥራት መጠን ሆኖ መመዝገቡን ጠቅሰው፤ በያዝነው ዓመት የሚገኘውን ገቢ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለቡና ዘርፉ ዕድገት ትልቅ ድርሻ ማበርከቱንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካለው የዓረቢካ ቡና ዝርያ 90 በመቶ የሚሆነውን የጄኔቲክ ብዝሃ-ህይወት በመያዟ ለዓለም የቡና ኢንዱስትሪ እንደ ዘር ባንክ እንደምትቆጠርም ተናግረዋል፡፡

ይህም ለተለዋዋጭ የአየር ንብረት የማይበገሩ ዝርያዎችን ለማምረት ልዩ ዕድል መፍጠሩን ተናግረው፤ ጥሬ ቡናን ከመላክ ባለፈ እሴት የተጨመረበት ቡናን ወደ ውጭ ለመላክ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና አማካኝነት በአህጉሪቱ ውስጥ የቡና ንግድን ለማጠናከር የፖሊሲ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር፤ መንግስት በቡናው ዘርፍ የጀመረው የሪፎርም ስራ አስደናቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።


 

ይህ የለውጥ እርምጃ ከአምራች አርሶ አደሩ ጀምሮ በንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ አካላትን ተጠቃሚነት በእጅጉ ማሳደጉን ገልጸዋል።

እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የቡና ገበያ ድርሻ እንድታሳድግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።

የአፍካ (AFCA) ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ጊልበርት ጋታሊ በዚሁ ጊዜ በአፍሪካ የቡና ዘርፍን ለማዘመንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማረጋገጥ ከአጋር ድርጅቶች ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።‎


 

በተጨማሪም ለላኪዎች፣ ለገዢዎች፣ ለማሽን አምራቾች፣ ለቡና ጥራት ባለሙያዎች እና በጥቅሉ በዘርፉ ኢንዱስትሪው የአቅርቦትና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ላሉ አካላት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንሱ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር የአፍሪካን የቡና ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም