ቀጥታ፡

የግብርና ዘርፉን በማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለመውጣት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የግብርና ዘርፉን በማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለመውጣት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ግብዓት ስርጭትን አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በወላይታ ሶዶ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሺእመቤት ነጋሽ፤ የግብርና ዘርፉን በማዘመንና ሜካናይዜሽንን ከማስፋት ባለፈ የግብአት አቅርቦቶችን በማሟላት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ግብን ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። 

ኮርፖሬሽኑ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲሁም ሌሎች ግብአቶችን በብዛትና በጥራት በማቅረብ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

እስከአሁኑ ሂደት 560 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች መድረሱን ጠቅሰው በዘርፉ ልማት የተያዘውን ግብ ለማሳካት በተደመረ አቅም መስራቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

በበጀት ዓመቱ ለምርጥ ዘር አቅርቦትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግብርና ግብዓት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግዳልቅ አልቅሚ፤ ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርበው ግብዓት በክልሉ የግብርና ሴክተር የተያዘውን ግብ ለማሳካት ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለዘርፉ ልማት ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራትና ውጤት ማምጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።


 

በኦሮሚያ ክልል ግብርና ግብዓቶች ምርት ጥራትና ቁጥጥር የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ጀቤሳ፤ በኮርፖሬሽኑ በኩል የግብዓት ስርጭት መኖሩ በጥራትና ምርታማነት ላይ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ከኮርፖሬሽኑ ጋር ባለ ጠንካራ የትብብር ግንኙነት የዘር ጥራት ቁጥጥር በማድረግ የተሻለ ውጤት ማምጣት መቻሉን አንስተው በዚህም የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም