ማህበሩ በደቡብ ሶዶ ወረዳ ከ284 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባቸው የልማት ፕሮጀክቶች ስራ ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በደቡብ ሶዶ ወረዳ ከ284 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባቸው የልማት ፕሮጀክቶች ስራ ጀመሩ
ወልቂጤ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር በምስራቅ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ ከ284 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባቸው የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የልማት ማህበሩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙስጠፋ ሃሰን፤ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ማህበሩ የማህበረሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት የሚደረጉ ጥረቶችን እያገዘ ነው።
በተለይም መንግስት እያካሔዳቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን በማገዝ ስኬታማ ስራዎች እየሰራ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
ከዚህ ውስጥም ከ284 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት የገቡ የልማት ስራዎችን በዛሬው እለት ለማሕበረሰቡ ማስረከቡን አብራርተዋል።
ማሕበሩ በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ በጤና እና ትምህርት የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ላይ የሚያከናውናቸው ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቅባቱ ተሰማ በበኩላቸው፤ ማህበሩ የአርሶ አደሩን ኑሮ በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ለአብነትም ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ በደቡብ ሶዶ ወረዳ 140 የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በትምህርትና በጤና እንዲሁም የግብርና ስራዎችን በማዘመንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚከናወኑ ተግባራት ለማገዝ ማህበሩ ቁርጠኛ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቀጣይም ማህበሩ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚደረጉ ተግባራትን ከማገዝ አንፃር የበኩሉን እንደሚወጣም ነው የጠቀሱት።
ማህበሩ ባስገነባው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና የጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች አቶ አስናቀ ጉግሳ እና አቶ ይርጋለም ቁምቢ ናቸው።
የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር በ2001 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወቃል።