ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ሥርጭት ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ሥርጭት ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ሥርጭት ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኢንዶክሬይንና ሜታቦሊዝም ማህበር ጋር በመተባበር አራተኛውን ዓመታዊ የጤና ጉባኤ አካሂዷል፡፡
በጉባኤው ላይ ጤና ሚኒስቴርን ወክለው የተገኙት በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ባለሙያ ዶክተር ሙሴ ገብረሚካኤል እንደገለጹት፤ የስኳር ሕመም መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጠባቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል ቀዳሚው ነው ብለዋል።
የስኳር ሕመም ከመከሰቱ በፊት የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከልና አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።
በሀገራዊ ለውጡ መንግሥት የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር የቅድመ መከላከል፣ የሕክምና አገልግሎትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ያካተተ ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ተግባር መግባቱንም ነው የገለጹት፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ጥቂት ባለሙያዎችን ይዞ የተመሠረተ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የባለሙያዎቹ ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
እስካሁን በዘርፉ ለተሰማሩ ከ600 በላይ የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የስኳር፣ የታይሮይድና የሆርሞን ሕመሞች ዙሪያ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በቀጣይም ማህበሩ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ድርጅቶች ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር ክፍተቶችን ለመሙላት በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።