ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱን የልህቀት ማእከል ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ይጠናከራሉ   

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩትን አቅምና አደረጃጀት በማጎልበት የልህቀት ማእከል የማድረግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ።  

የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት የሪፎርም፣ የአዲስ ሎጎ ማስተዋወቂያና በፍትህ ዘርፉ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎችና አመራሮች እውቅና የመስጠት መርሃግብር የፍትህ ዘርፍ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

በመርሃግብሩ ላይ  የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ በአዲስ አደረጃጀት ወደ ስራ ገብቷል።


 

ኢንስቲትዩቱ ተጠሪነቱ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደረጉ የምርምርና  የስልጠና ስራዎች ከፍትህ አካላት ጋር በተጣጣመና በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል።

አደረጃጀቱ የተቋሙን አገልግሎት ለማሻሻልና ለማቀላጠፍ እንዲሁም የህግ አወጣጥና አፈጻጸም ችግሮችን ለመፍታት የተቋሙን አቅም የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱን የአቅም ግንባታ፣ የምርምርና የመረጃ ማእከል ስራዎችን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት አዲስ ሎጎ ይፋ የተደረገ ሲሆን ይህም የኢንስቲትዩቱን የልህቀት ማዕከልነት ለማጎልበት ከሚከናወኑ ስራዎች ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል።


 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበባ እምቢያለ በበኩላቸው፤ የኢንስቲትዩቱና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትብብር ማእቀፍ እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተዋል።


 

ይህም በፍትህ ሰርዓቱ የሚከናወኑ የለውጥ ስራዎች ጠንካራ የምርምርና የፖሊሲ መሰረት እንዲኖራቸውና ኢንስቲትዩቱን የልህቀት ማእከል ለማድረግ የሚከናወኑ ስራዎች ላይ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። 

የፌዴራል ህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት  ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ እንደተናገሩት፤  ኢንስቲትዩቱ መዋቅራዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ወደ ሁሉ አቀፍ የለውጥ ምእራፍ ተሸጋግሯል ።


 

የሶስት አመታት ፍኖተ ካርታና ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በኢንስቲትዩቱ ከ80 በላይ ጥናቶችና ምርምሮች  መካሄዳቸውን ገልጸው፤  በፍትሐብሔር ፣ በወንጀል ፣ባህላዊ ፍትህ አስተዳደር ፣ ሰብአዊ መብትና ሌሎች  ጉዳዮች ለይ ምርምር ከተከናወነባቸው ጉዳዮች መካከል  ለአብነት ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዓመታት ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የፍትህ ዘርፍ ባለሙያዎችና አመራሮች ስልጠና መሰጠቱንም አክለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ዘመኑ የሚጠይቀውን የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ የልህቀት ማእከል  ለመሆን እየሰራ  ነው ብለዋል።

የስልጠና ማእከሉን ምቹ የማድረግ ፣ የኢ-ለርኒንግ ስቱዲዮ የማዘጋጀት ፣ የመረጃ ማእከል የማደራጀት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም