የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የሙስና ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የሙስና ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፡- የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ የሙስና ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በተቋማት የሚያካሂደው የሙስና ተጋላጭነት ጥናቶች የመከላከል ስራውን ውጤታማነት ማሳደጉንም ተጠቁሟል፡፡
መንግስት በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚፈጸሙ የሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና መሰል ድርጊቶችን ለመከላከል የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
በዚህ ረገድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ሙስናን ከመከላከልና ግልጽነትን ከመፍጠር አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፉ ማድረጋቸው ለብልሹ አሰራር የሚመች ሁኔታን ማጥበብ ይቻላል፡፡
ይህ የዲጂታላይዜሽን ስራ ዜጎች ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገም ይገኛል፡፡
ይህ ተግባር በፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እየተካሄደ ካለው የሙስና ተጋላጭነት የልየታ ጥናት ጋር ተዳምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የፀረ-ሙስና ንቅናቄ ይበልጥ ውጤታማ እያደረገው ይገኛል።
በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ጥናት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ ጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ለሙስና ወንጀል ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን በማሻሻል ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በተለይም በዜጎች ፍትሃዊ የአገልግሎት ተጠቃሚነት ላይ እንቅፋት የሆኑ ብልሹ አሰራሮችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የልየታ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት በ14 ተቋማት ላይ ጥናት ተካሂዶ ግብረ-መልስ ተሰጥቷል።
ጥናቶቹ ቁልፍ በሆኑ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የሙስና ተጋላጭነት መንስኤዎችን በግልጽ የሚያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው ጥናቱን ተከትሎ ተቋማት አሰራራቸውን እንዲፈትሹ ከማድረግ ባለፈ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የተቋማት የሕግ ማሻሻያ፣ የአደረጃጀት ለውጥና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲዘረጉ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የጥናት ውጤቶቹ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰው ኮሚሽኑ እርምጃዎቹ በአግባቡ መወሰዳቸውን በጥብቅ ይከታተላል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋማት የተቀናጀና የተቀላጠፈ ስራ እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አሰራሩም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ዜጎች ያለእንግልት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ የጥናትና የማሻሻያ ስራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እያገዙ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡