አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) ወጥነት ያለው የአሰራርን በማስፈን ዘመናዊ የክትትል ስርዓት ለመዘርጋት ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) ወጥነት ያለው የአሰራርን በማስፈን ዘመናዊ የክትትል ስርዓት ለመዘርጋት ያግዛል
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) ወጥነት ያለው የአሰራር ስርዓትን በማስፈን ዘመናዊ የክትትል ስርዓት ለመዘርጋት ያግዛል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአይነቱ ለየት ያለ አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ፣ ተቋሙ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
በሪፎርሙ በተለይም የተቋሙን አሰራር በቴክኖሎጂ ማዘመን በመቻሉ በወንጀል መከላከል ረገድ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳም ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የተቋሙን የመፈጸም አቅም በእጅጉ የሚያልቅ መሆኑን አንስተዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) ወጥ የሆነ ቁጥጥር ለማድረግ ምቹ እንዳልነበር አውስተዋል።
አዲሱ ታርጋ የፌደራል ፖሊስን መለያ ምልክት፣ ሚስጥራዊ ኮድንና ዲጂታላይዜሽንን ያካተተ መሆኑ ከቀድሞው ለየት ያለ እና ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀ ነው ብለዋል።
በዚህም ወጥነት ያለው የአሰራር ስርዓት በማስፈን ዘመናዊ የክትትል ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያግዝ አመላክተዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በረኦ ሀሰን በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ተመዝግበው ይገኛሉ ብለዋል።
የእነዚህን ተሽከርካሪዎች ስምሪት በአግባቡ ለማስተዳደር ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና አሰራሩን ማዘመን ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በቅርቡም አዲሱን ሀገር አቀፍ የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዛሬው እለት ይፋ ያደረገው አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ የተቋሙን የሪፎርም ጉዞ ስኬት የሚያሳይ መሆኑንም ገልፀዋል።