የመድሃኒት አቅርቦትና ፍላጎትን በማጣጣም ለሕብረተሰቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመድሃኒት አቅርቦትና ፍላጎትን በማጣጣም ለሕብረተሰቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ ነው
ገንዳውኃ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን የመድሃኒት አቅርቦትና ፍላጎትን በማጣጣም ለሕብረተሰቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የጤና መድህን አስተባባሪ አዛናው ታከለ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በሽታን ቀድሞ በመከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ እየተሰራ ነው።
የህክምናና የመድሃኒት አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት የዞኑ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል።
ሕብረተሰቡ የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆንና የህክምና አገልግሎትን በፍጥነት እንዲያገኝ እየተሰራ ባለ ሥራም ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል።
በዞኑ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች በተደጋጋሚ ያነሱት የነበረውን የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት እርምጃዎች መወሰዳቸውን አንስተዋል።
የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል በገንዳውኃ፣ በመተማ ወረዳ ኮኪት ከተማና በቋራ ወረዳ የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን ማቋቋም አንዱ ነው ብለዋል።
የመድሃኒት ቤቶቹ መቋቋም የመድሃኒት አቅርቦትና ፍላጎትን በማጣጣም ለሕብረተሰቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል ነው ያሉት።
የማሕበረሰብ መድሃኒት ቤቶችን በቅርቡ በአዳኝ አገር ጫቆና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች እንዲሁም መተማ ዮሃንስና ምድረ ገነት ከተሞች ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል።
የማሕበረሰብ መድሃኒት ቤት ተጠቃሚዎች መካከል የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዋ ውብነሽ ታደሰ አንዷ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ በማሕበረሰብ መድሃኒት ቤቱ ሌላ ቦታ ፈልገው ያላገኙትን መድሃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ችለዋል።
በመደበኛነት የሚወስዱትን መድሃኒት በግል መድሃኒት ቤቶች ከፍተኛ ዋጋ በማውጣት ይገዙ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ ወርቁ ብላታ ናቸው።
የማሕበረሰብ መድሃኒት ቤቶቹ ከተቋቋሙ በኋላ መድሃኒታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ወጪያቸውን እንደቆጠቡ አመልክተዋል።