ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መንግስት ለዜጋ እና ለሀገር ያለውን ክብር ያሳየበት ልዩ እሳቤ እና ትግበራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፡-የሌማት ትሩፋት መንግስት ለዜጋ እና ለሀገር ያለውን ክብር ያሳየበት ልዩ እሳቤ እና ትግበራ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት በሌማት ትሩፋት ዘላቂ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ፖሊሲ ትግበራ ተደማሪ አቅም በማድረግ ሰርቷል ብለዋል፡፡


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምዕናብ ልህቀት ፈልቆ የተጀመረው ኢኒሼቲቭ የብዙ ቤተሰብን ሕይወት ቀይሯል፣ ደግሞም ወደፊትም መቀየሩን ይቀጥላልም ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ለዘመናት ጸጋ ሆነው ያልታዩ ጓሮዎችን የልማት ከባቢ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የተመጣጠነ ምግብ በሽታ መከላከልን ካስቀደመው የጤና ፖሊሲያችን ጋር ግንኙነቱ ቀጥተኛ ነው፡፡ በዚህም የመደመር እሳቤ ባፈለቀው የፈጠራ ተግባር የእንስሳት ተዋጽኦ በአግባቡ ወደ ሌማታችን አምጥቷል፡፡


 

የሌማት ትሩፋት የተሳሰረው ከከበረ የሰዎች ከሕይወት እና ጤና እንዲሁም ከትልቁ የሃገር መልክ እና ክብር ብሎም ከዘላቂ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ርዕያችን ጋር ነው ያሉት አቶ ተመስገን፥ በትጋት የሚሰሩ ክንዶች ሌማታቸውን አትረፍርፈዋል ወደፊትም ያትረፈርፋሉ በማለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም