ቀጥታ፡

በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት 40 የውሃ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ማዳረስ ተችሏል   

ወልዲያ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ በሰሜን ወሎ ዞን በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 40 የውሃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ከ65 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ማዳረስ መቻሉን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ፋሲል አረጋ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው።

በዘጠኝ ወረዳዎች የ124 አነስተኛና ከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ 115 አነስተኛ ቀሪዎቹ ደግሞ ከፍተኛ የውሃ ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።


 

ከነዚህ መካከል ባለፉት ስድስት ወራት የ34 አነስተኛና የስድስት ከፍተኛ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አመልክተዋል።

በዚህም ከ65 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃን ማዳረስ ተችሏል ነው ያሉት።

በእነዚህ ፕሮጀክቶች ምክንያት በዞኑ በከተማና በገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ቀሪ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታን በማፋጠን የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ርብርብ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ከንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎቹ መካከል የሐብሩ ወረዳ ነዋሪዋ  ዘምዘም አልዩ እንዲሁም የጉባላፍቶ ወረዳ ነዋሪው ደስታው አየነ ይገኙበታል።


 

እነርሱ እንደሚሉት፣ በአካባቢያቸው የተገነቡ ፕሮጀክቶች ያጋጥማቸው የነበረውን የውሃ እጥረት ችግር ከማቃለል ባለፈ ድካምና እንግልትን አስቀርቷል።

በሌላ በኩል በእነርሱና በቤተሰባቸው ላይ ይደርስ የነበረውን የውሃ ወለድ በሽታ የሚከላከል መሆኑን ተናግረዋል።

ለውሃ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም