ቀጥታ፡

የታዳሽ ሃይል አማራጭን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሎካ አባያ ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የታዳሽ ሃይል አማራጭን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይልን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሲዳማ ክልል ሎካ አባያ ወረዳ 632  ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ የጸሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቋል።

በወቅቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የታዳሽ ሃይል አማራጭ በመጠቀም ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።


 

በዚህም ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን እስከ ቀጣዮቹ ሁለት አመታት 100 የጸሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት ይጀምራሉ ብለዋል።

በዚህም ከ130 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸው አንድ ሺህ 400 ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን የጸሃይ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ምቹ ባልሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለታዳሽ ሃይል አማራጭ ትኩረት መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው፤አገልግሎቱ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀት ላይ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን የጸሃይ ሃይል ማመንጫ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት ከ22 በላይ የጸሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ከ5 ሺህ 137 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።


 

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ16 በላይ የጸሐይ ሃይል ማመንጫዎች ተመርቀው አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

የመረራ የጸሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 632 ኪሎ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ በበኩላቸው፤ በክልሉ አምስት የጸሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።


 

ዛሬ የተመረቀው የመረራ የጸሐይ ሃይል ማመንጫ ከነዚህ አንዱ ሲሆን ከ2 ሺህ 500 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የጸሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ መመረቅ የአካባቢውን ህዝብ የቆየ የኤሌክትሪክ ሃይል ጥያቄን የሚፈታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሎካ አባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲዳሞ ኩሚሳ ናቸው።

በምረቃ መርሃ ግብሩ የአካባቢው ነዋሪዎችና የተለያዩ የመንግስት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም