የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና ዳኞችን ሹመት አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና ዳኞችን ሹመት አፀደቀ
አዲስ አበባ፤ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና 50 የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አፀደቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ በ11ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አፅድቋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን የስራ ልምድ ባቀረቡበት ወቅት ተሿሚዎች በትምህርት ዝግጅታቸው እና በስራ ልምዳቸው ለፍትህ ስርዓቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እየተካሄደ ባለው የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ አስተማማኝ የዳኝነት ስርዓትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በፍርድ ቤቶች ዘመናዊ፣ ግልጽ፣ ነጻና ገለልተኛ አሰራር በመዘርጋት ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና 50 የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመትን አፅድቋል፡፡
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ በቀረቡለት ዕጩዎች ላይ ተወያይቶ የአቶ ልዑል ካህሳይን እና የአቶ ምትኩ ማዳን ሹመት ውሳኔ ቁጥር 6/ 2018 አድርጎ አጽድቋል።
በተመሳሳይም ምክር ቤቱ በቀረቡለት 50 የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞች ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ የቀረቡለትን ዕጩዎች ሹመት የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 7/2018 በማድረግ አጽድቋል።