የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች በተመጣጣኝ ክፍያ የጤና አገልግሎትን ለማቅረብ የማይተካ ድርሻ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች በተመጣጣኝ ክፍያ የጤና አገልግሎትን ለማቅረብ የማይተካ ድርሻ እያበረከተ ነው
ጅማ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የጤና መድህን አገልግሎት ለዜጎች በተመጣጣኝ ክፍያ የጤና አገልግሎትን ለማቅረብ የማይተካ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ በጅማ ከተማ እያካሄደ ይገኛል፡
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ያምሮት አንዷለም በወቅቱ እንዳሉት የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች በተመጣጣኝ ክፍያ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የማይተካ ድርሻ እያበረከተ ነው።
የህክምና አገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋትም በሀገሪቱ 63 ሚሊዮን አባላትን ማፍራት መቻሉን አንስተዋል።
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ትዕግስት ተፈሪ በበኩላቸው በክልሉ የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል የጤና ተቋማትን አቅም በማሳደግ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ሀብታቸውን ሳያባክኑ ጥራት ያለው ሕክምና እንዲያገኙ እያገዘ በመሆኑ ተግባሩን ለማስፋት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ በበኩላቸው በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆነውን ህብረተሰብ በማገዙ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አገልግሎቱ ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ የሀብት ማሰባሰብ ቡድን መሪ አቶ ጸጋዬ ታዲዮስ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ በርካታ ዜጎች የጤና መድህን ተጠቃሚ ሆነዋል።
በመድረኩ ከተለያዩ ክልሎች ከመጡ የጤናው ዘርፍ ሀላፊዎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው::