የቡና ወጪ ንግድን ይበልጥ ለማሳደግ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ወጪ ንግድን ይበልጥ ለማሳደግ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የቡና ወጪ ንግድን ይበልጥ ለማሳደግ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለውጪ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከምስራቅ አፍሪካ ፋይን ኮፊ ማህበር (AFCA) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 22ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ (Africa Fine Coffee) ኤግዚቢሽንና ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 469ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ገልጸዋል፡፡
ይህ ውጤት በሀገሪቱ የቡና ታሪክ ከፍተኛው የገቢና የጥራት መጠን ሆኖ መመዝገቡን ጠቅሰው በያዝነው ዓመት የሚገኘውን ገቢ ወደ 3 ቢሊየን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለቡና ዘርፉ ዕድገት ትልቅ ድርሻ ማበርከቱንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካለው የዓረቢካ ቡና ዝርያ 90 በመቶ የሚሆነውን የጄኔቲክ ብዝሃ-ህይወት በመያዟ ለዓለም የቡና ኢንዱስትሪ እንደ የዘር ባንክ እንደምትቆጠርም ተናግረዋል፡፡
ይህም ለተለዋዋጭ የአየር ንብረት የማይበገሩ ዝርያዎችን ለማምረት ልዩ ዕድል መፍጠሩን ነው የተናገሩት፡፡
ጥሬ ቡናን ከመላክ ባለፈ እሴት የተጨመረበት ቡናን ወደ ውጪ ለመላክ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና(AfCFTA) አማካኝነት በአህጉሪቱ ውስጥ የቡና ንግድን ለማጠናከር የፖሊሲ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡
ኮንፍረንሱ የአፍሪካ ቡና አምራቾችን ከዓለም አቀፍ ገዢዎች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ የማድረግ ብሎም የንግድ ሰንሰለቱን ፍትሐዊ ለማድረግ እንደሚረዳም ነው የጠቆሙት፡፡
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ሁመር እንደገለጹት፤ መንግስት በቡናው ዘርፍ የጀመረው የሪፎርም ስራ አስደናቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
ይህ የለውጥ እርምጃ ከአምራች አርሶ አደሩ ጀምሮ በንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ አካላትን ተጠቃሚነት በእጅጉ ማሳደጉን ገልጸዋል።
የዘርፉን የኢኮኖሚ አቅም ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ አሁን እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የቡና ገበያ ድርሻ እንድታሳድግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።