የሴፍቲኔት ፕሮግራም የሥራ ባህላችንን ለማሳደግ አግዞናል- በኮምቦልቻ ከተማ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሴፍቲኔት ፕሮግራም የሥራ ባህላችንን ለማሳደግ አግዞናል- በኮምቦልቻ ከተማ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች
ኮምቦልቻ ፤ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፡- የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ጥሪት ለማፍራትና የሥራ ባህላቸውን ለማሳደግ እንዳገዛቸው በኮምቦልቻ ከተማ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ገለፁ።
በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በከተማ ሴፍቲኔት ታቅፈው ህይወታቸውን የለወጡ 1 ሺህ 268 ተጠቃሚዎች ዛሬ ተመርቀዋል።
ከፕሮግራሙ ተመራቂዎች መካከል አቶ ዳንኤል አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት የሚሰራ ጉልበትና የስራ ፍላጎት ቢኖራቸውም በገንዘብ እጥረት በችግር ውስጥ መቆየታቸውን አስታውስዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍም በሴፍቲኔት መርሃ ግብር አረንጓዴ ልማት ተሰማርተው ገቢ ከማግኘታቸው ባሻገር በአትክልት ልማት ተሰማርተው አኗኗራቸው እንዲለወጡ እንዳገዛቸው ገልጸዋል።
ከአትክልት ልማቱ ካገኙት ገቢም ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር አልፈው ወደ ፍየል እርባታ ስራ ለመሸጋገር ማቀዳቸውን አስረድተዋል።
ሌላዋ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ወይዘሮ ትግስት ጫኔ በበኩላቸው በፕሮግራሙ የከተማውን ውበትና ልማት ከመጠበቅ ባለፈ በተመቻቸላቸው የገቢ ማስገኛ ሥራ ሀብት ማፍራት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በከተማው የቆሻሻ መጣያ የነበሩ አካባቢዎችን በማጽዳት ድንች፣ ሽንኩርትና ሌሎች አትክልቶችን በማልማት በሚያገኙት ገቢ ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብና ባገኙት ድጋፍ በመታገዝ በእንጀራ መጋገር ሥራ ተሰማርተው ለምግብ ቤቶችና ለሌሎችም እያስረከቡ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ታቅፈው በተመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታና የሥራ እድል ከችግርና ከተረጂነት ተላቀው እራሳቸውን መቻላቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ተጠቃሚ አቶ ማዘንጊያ በለጠ ናቸው።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራሁ አሰግደው እንደገለጹት ባለፉት ሶስት ዓመታት በፕሮግራሙ የታቀፉ 1 ሺህ 268 የቤተሰብ መሪዎች ዛሬ ተመርቀዋል።
በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት፣ በግንባታና ሌሎች ልማቶች በመሰማራት ምርታማነታቸውን በማሳደግና ከተረጂነት በመውጣት ጥሪት ማፍራት መቻላቻውን አስገንዝበዋል።
የሥራ ተነሳሽነታቸውን በማሳደግና የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ ከራሳቸው ተርፈው ሌሎችን በመደገፍ ምሳሌ መሆን መቻላቸውንም ገልጸዋል።
የከተማው ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ በበኩላቸው፤ ዛሬ ከፕሮግራሙ ለሚመረቁ ዜጎች የመስሪያ ቦታና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
በምረቃ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ከተማና መሰረት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ በርካታ ዜጎችን በምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ፕሮግራም በማቀፍ ከድህነት እንዲወጡ ተደርጓል።
በከተማ ግብርና፣ በእንሰሳት እርባታና ማድለብ፣ በሌማት ትሩፋትና ሌሎች የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግም ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በምረቃ ፕሮግራሙ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።