ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ሴቶች በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ሴቶች በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል
ጎንደር ፤ጥር 28/2018(ኢዜአ)፡- ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የብድር አገልግሎትና የስራ እድል ተጠቃሚ እንድንሆን አስቻይ ሁኔታን ፈጥሮልናል ሲሉ በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሴቶች ገለጹ፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ከ183 ሺህ በላይ ሴቶች የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ማውጣታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እታገኝ ፈጠነ፤ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ማውጣቴ በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ ለመሆን አስችሎኛል ነው ያሉት።
ከዚህ ውስጥም ብድር በማግኘት የግል ስራቸውን ለማከናወን ከመቻላቸውም ባለፈ በመንግስት ተቋማትም ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ነው የሚያስረዱት፡፡
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ቸርነት ጌታቸው በበኩላቸው የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ አካል ጉዳተኞች የመንግስት አገልግሎትን ለማግኘት ይገጥመን የነበረውን እንግልትና ውጣ ውረድ ያስቀረ ነው ብለዋል፡፡
መታወቂያውን በማውጣትና የአካል ጉዳተኞችን በማህበር በመደራጀታችን ከከተማ አስተዳደሩ የመስሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ወደ ስራ ገብተናል ሲሉ ገልጸዋል።
የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ የዜግነት ማረጋገጫ ከመሆን ባለፈ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጹት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ብርቱካን ብርሃኑ ናቸው፡፡
በተለይም ሴቶች ያለ ንብረት ማስያዣ ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መልካም እድሎችን በመፍጠሩ የብድር አገልግሎት አግኝተው የግል ስራቸውን ለማከናወን እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡
በጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ተከታይ ጫቅሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከ183 ሺህ በላይ ሴቶች ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ወስደዋል ነው ያሉት።
ያለፉት ስድስት ወራት አፈፃፀም በእቅድ ከተያዘው በ10 ሺህ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመው አስከ በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያም ከ242 ሺህ በላይ ሚሆኑ ሴቶች የፋይዳ መታወቂያን እንዲያወጡ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለፓርላማ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በሌሎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆኗን መናገራቸው ይታወሳል።