ቀጥታ፡

ለዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ እውን መሆን የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት ድርብ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ ለዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ እውን መሆን የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት ድርብ መሆኑን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24/2018 ዓም ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ ሲሆን የዕጩዎች ምዝገባም እየተከናወነ ይገኛል።

በመጪው ጠቅላላ ምርጫ የመገናኛ ብዙሃን ድርሻን አስመልክቶ ኢዜአ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህራንን አነጋግሯል።

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ተሻለ ተገኔ(ዶ/ር) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የምርጫ ህጉን በተመለከተ ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።


 

በምርጫ ወቅት መራጮች በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው ድምጽ እንዲሰጡ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አክለዋል።

የምርጫው ሂደት ትክክለኛ፣ ዴሞክራሲያዊና አካታች መሆኑን በመከታተልና የተቀመጡ የስነ ምግባር መርሆዎችን ተከትሎ መረጃ በመስጠት ህዝቡ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ሂደቱን በመከታተል ለመራጩ ህዝብ ግንዛቤ በመፍጠር ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በሚበጅ መልኩ አበክረው መስራት እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።


 

ምርጫው ተዓማኒ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ወገኔ ዳንኤል ናቸው።

መገናኛ ብዙሃን እና የሚዲያ ባለሙያዎች በምርጫ ዘገባ ወቅት ሙያዊ የስነ ምግባር መርሆዎችን ተከትለው የመስራት ግዴታ እንዳለባቸውም ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም