በኩታ ገጠም ኮረሪማን በማልማት የመሎኮዛ ወረዳ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኩታ ገጠም ኮረሪማን በማልማት የመሎኮዛ ወረዳ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል
ሳውላ ፤ጥር 28/2018 (ኢዜአ) ፡-በኩታ ገጠም ኮረሪማን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን በጎፋ ዞን የመሎኮዛ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
ከደጋ እስከ ቆላ አየር ንብረት የያዘው የጎፋ ዞን ቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ ፍራፍሬና የተለያዩ ሰብሎችን ለማምረት የሚያስችል ዕምቅ ሀብት የያዘ ሲሆን በተለይ በደጋማ አካባቢዎች በስፋት ኮረሪማ ይመረትበታል።
በዞኑ ኮረሪማ አምራች ከሆኑት ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የመሎኮዛ ወረዳ ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኮረሪማ ተሸፍኗል።
በወረዳው ኮረሪማ ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች መካከል ሞዴል አርሶ አደር ደነቀ ጎሹ አንዱ ናቸው፤ አርሶ አደሩ በኮረሪማና ቅመማ ቅመም ካለሙት አምስት ሄክታር መሬት 30 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ኮረሪማን በኩታ ገጠም የእረሻ ስነ-ዘዴ በማከናወናቸው ምርታማነታቸውን ማደጉን ተናግረዋል።
በዚህም አንድ ኩንታል ኮረሪማን ከ150 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር በመሸጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው መላቁንም አክለዋል።
በዚህም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ከመገንባት ባለፈ ተጨማሪ ገቢ የሚያመነጭ ወፍጮ በመትከል እየሰሩ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ምርታማነቱ የተሻሻለ የኮረሪማ ቅመም በ2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር አርሼ ዘለቀ ናቸው።
ከልማቱም በዓመት እስከ 30 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆኑን ተናግረው በኩንታል ከ150 ሺህ ብር በላይ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
የመሎኮዛ ወረዳ ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ አገኘሁ እንዳሉት በወረዳው በኮረሪማ ልማት ከተሸፈነው 15 ሺህ 520 ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ሺህ 700 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የለማ ነው።
በወረዳው ከለማው ኮረሪማ በዓመት 116 ሺህ ኩንታል እንደሚሰበሰብ ገልጸው ውጤታማነቱን ለማሳደግም ለአርሶ አደሩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከማቅረብ ባለፈ ድጋፍና ክትትል መደረጉን አንስተዋል።
በጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የቡናና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑርአዲስ አደም እንዳሉት በዞኑ መሎኮዛ፣ ገዜ ጎፋና ሌሎች ደጋማ አካባቢዎች ኮረሪማ በስፋት ይመረታል።
አርሶ አደሩ ምርቱን በስፋት ማምረት እንዲችል በባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝና ከጊዜ ወደ ጊዜ የማሳ ሽፋኑ እያደገ እንደመጣ ጠቁመዋል።
በገበያ ያለው ዋጋ እያደገ መምጣቱ ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተናገሩት አቶ ኑርአዲስ ከዞኑ በተያዘው ዓመት ከ30 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እስካሁን ከ8 ሺህ ቶን በላይ ለገበያ መቅረቡን ገልጸዋል።