ቀጥታ፡

በግማሽ ዓመቱ 63 አዳዲስ የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ በግማሽ ዓመቱ 63 አዳዲስ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው የስድስት ወራት አፈጻጸምን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ በዘርፉ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

በግማሽ ዓመቱ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ከማድረግ በኩል ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቅሰው፤ 63 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ወደ ኃይል መስመር መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የገጠር ቀበሌዎቹን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው ከዋናው መስመርና ከፀሐይ ኃይል መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

ይህም የገጠሩን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ይህንን አፈጻጸም ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙ ደንበኞች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከተለያዩ የገቢ አማራጮች 52 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም