ቀጥታ፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሐረር፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰሠሩ መሆኑን በሐረሪ ክልል በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመንግስትን የ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜ መንግስት ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ አካታች እንዲሁም ከባለፈው ምርጫ በሁሉም መስፈርት የተሻለ እንዲሆን አበክሮ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በሐረሪ ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እያደረጉት ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮዽያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ(ኢብአፓ) የሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር አስተባባሪ ሐሰነት ሙሜ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋትና የመድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን ለማጠናከር የጋራ ምክር ቤት መመስረታቸውን አስታውሰዋል።

የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንጠቁመው በዚህም ምክር ቤቱ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚናውን ተጫውቷል ብለዋል።

አክለውም ምክር ቤቱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለፓርቲ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ አሁን ላይ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች ፓርቲዎችንም የምክር ቤቱ አባል ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዳይሬክተር ሐሰን አብዲ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከተደረጉ ምርጫዎች በተሻለ መልኩ አሳታፊ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህም ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የድርሻውን መወጣቱን አስታውሰዋል።

አቶ ሐሰን አክለውም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መመዘኛዎች ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ አሳታፊ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና የክልሉ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ(ነእፓ) ምክትል ሰብሳቢ አብዱልሃፊዝ አህመድ ፓርቲያቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ የድርሻቸውን ከሚወጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ምርጫ እንደመሆኑ ጠቅላላ ምርጫው ሁሉን አሳታፊና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም