ቀጥታ፡

በመግባባት ላይ የተመሰረተ የምክክር ሂደት ማካሄድ ለዘላቂ ሰላም ዋጋ መስጠት ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር በመግባባት ላይ የተመሰረተ የምክክር ሂደት ማካሄድ ለዘላቂ ሰላም ዋጋ መስጠት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራር አባላት ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።


 

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የተከናወኑ ተግባራትን ገለፃ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የግጭት አዙሪት የተሳሳቱ መንገዶች በሀገራዊ ምክክር መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚገባ የዘመናት ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት ምክክር አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፥ ምክክርም በመግባባት ላይ የተመሰረተ ሂደትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በዚህም የአማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ መካሄዱን ገልጸዋል።

የነፍጥ ትግል አሸናፊና ተሸናፊን የሚፈጥር እንጂ ሀገራዊ መግባባትን የሚያሰፍን እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

ታጣቂ ኃይል የትጥቅ ትግልን አስከፊነት በቅጡ በመገንዘብ ለዘላቂ ሰላም ዋጋ ይሰጣል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፥ አጀንዳዎችን በመለየት በምክክር መፍትሔ ያገኛሉ በሚል ለወሰዱት ቁርጠኛ አቋም ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ምክትል ሊቀመንበርና ወታደራዊ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ፥ የትጥቅ ትግል ህዝብን ከማጎሳቆል ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው በመገንዘብ የሰላም ስምምነት መውሰዳቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ለትጥቅ ትግል መነሻ የነበሩ ጉዳዮችን በመሰነድ ለአማራ ህዝብና ኢትዮጵያ ችግር የሆኑ አጀንዳዎች በምክክር መፍትሔ እንደሚያገኙ በማመን ለይተው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእስካሁኑ ክንውኖች የተደረገላቸው ገለፃም በዜጎች መካከል ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ሂደቶችን እንዳለፈ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የውጭ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ፥ የሶስት ዓመታት የትጥቅ ትግላቸውን በሚገባ በማጤን አሉኝ የሚሏቸውን ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ለማስገኘት የሰላም አማራጭን እንደተከተሉ ገልጸዋል።


 

የተሳሳተ ትርክት፣ የሕገመንግስት እና ተያያዥ ጉዳዮች የተካተቱባቸውን አጀንዳዎች በማደራጀት በጋራ የምክክር መድረክ መግባባትን በመፍጠር በሂደት መፍትሔ እንደሚያገኙ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ፥ ከመንግስት ጋር ከደረሱት የሰላም ስምምነት በተጨማሪ አሉኝ የሚሏቸውንና እንዲፈቱ የሚፈልጓቸውን የተቆጠሩ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

ዓመታትን በተሻገረው የግጭት ቆይታቸው ህዝብን ከማጎሳቆል የዘለለ ፋይዳ እንዳልሰጠ ገልጸዋል።

በቀጣይም በሰላማዊ አማራጭ ለህዝብ ተጠቃሚነትና ኢትዮጵያ ህልውና በሚበጁ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ሌሎች በጫካ የሚገኙ ቀሪ ታጣቂዎችም የሰላም አማራጭን በመከተል ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም