በክልሉ የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወሳኝ ሚናን ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወሳኝ ሚናን ይጫወታል
ባህርዳር፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ የተዘጋጁ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት (PMS) እና የቁልፍ ተግባራት አፈፃፀም አመላካቾች (KPI) መተግበሪያዎች ስራ ማስጀመሪያ መድረክ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀመረ።
በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ተለዋዋጭ በሆነው አለም ቴክኖሎጂን ማልማትና መጠቀም ወሳኝ ነው።
በክልሉ የተያዙ የልማት ግቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻልና የሀብት ብክነትን ለመከላከል የሚያስችሉ መተግበሪያዎች መበልጸጋቸውን ተናግረዋል።
መተግበሪያዎቹ እንዲሁም የተቋማትን የተግባራት አፈፃፀም ጥንካሬና ድክመቶችን የሚያመላክቱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ክልሉ ቴክኖሎጂን በማልማትና በመጠቀም ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚለሙ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ የቻለ ይግዛው በበኩላቸው፣ በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን ለይቶና አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ቴክኖሎጂ ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ለቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
ይፋ የተደረጉ መተግበሪያዎችም የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓትን በማዘመን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲፈጸሙ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
የመንግስት የልማት ስራዎች በተቀመጠላቸው ዕቅድ መሰረት ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ሃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) ናቸው።
በማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ በግል ኢንቨስትመንትና የመረጃ ሥርዓት ዋና ዋና ቁልፍ ተግባራት ተለይተው ፍትሃዊነትን ለማስፈን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረግ ተቋማትን በውጤት ለመለካት የሚያስችል ሲሆን ዕቅድና ሪፖርታቸውን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመከታተል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በመድረኩ የተቋማት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን የለሙት መተግበሪያዎች ቀርበው ውይይት እየተደረገ ይገኛል።