ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ኬንያ የሁለትዮሽ የመከላከያ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ በስኬት ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ እና ኬንያ የሁለትዮሽ የመከላከያ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያና ኬንያ የመከላከያ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው 1ኛ መደበኛ የኢትዮ-ኬንያ የመከላከያ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ በስኬት ተጠናቋል።

በመተማመን፣ በመከባበርና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ እና የኬንያ መከላከያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን የኢትዮጵያን መከላከያ ልዑክ የመሩት የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬከተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ገልፀዋል።


 

ሜጄር ጄኔራል ተሾመ በውይይቱ ወቅት የቀረቡ አጀንዳዎች የሁለቱን ሀገራት የአጋርነትና የአብሮነት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ከመሆናቸውም በላይ የቀጣናው አሁናዊ ሁኔታ የሚጠይቀውን የጋራ ተሳትፎ አስመልክቶ ጠንካራ አቋም እንዲያዝ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን አንስተዋል ብለዋል። 

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በጠንካራ የሁለትዮሽ ትብብራችንና ውጤታማነታችን በማያስደስታቸው አካላት እኩይ ተግባር ሳንዘናጋ የየበኩላችንን መወጣት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።


 

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መከላከያ የበኩሉን ድርሻ በተመለከተ በኃላፊነት ስሜት፣ በትጋትና በውጤታማነት መወጣት የሚያስችል የላቀ ዝግጁነት እንዳለውም አረጋግጠዋል።

የኬንያ የመከላከያ ኦፕሬሽን፣ ኢንዶክትሪኔሽን እና ስልጠና ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሉዋሬ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት ለዘመናት የቆየ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ከመሆናቸው በላይ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በኢነርጂ ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አስረድተዋል።

 


 

ይህ መድረክ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ የሰላም እና ጸጥታ ዘርፎች የሚደረገውን ግንኙነት እና ትብብር በማጠናከር በኩል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አስገንዝበዋል።

#Ethiopian_News_Agency 
#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም