የአዲስ አበባ ከተማ የተለወጠ የስራ ባህል የከተማዋን ኢኮኖሚ 24 ሰዓት እያንቀሳቀሰ ይገኛል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ የተለወጠ የስራ ባህል የከተማዋን ኢኮኖሚ 24 ሰዓት እያንቀሳቀሰ ይገኛል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ የተለወጠ የስራ ባህል የከተማዋን ኢኮኖሚ 24 ሰዓት እያንቀሳቀሰ እና በርካታ የስራ እድሎችም እየፈጠረ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ
ከንቲባ አዳነች በካዛንችስ አካባቢ የሚገነባውን የህጻናት አለም ፓርክ እና በቦሌ መድኃኔዓለም እና 22 አካባቢ የሚገነቡ የኮሪደር ልማት አገናኝ መስመሮችን የምሽት የስራ እንቅስቃሴ ገምግመዋል።
አዲስ አበባ ከተማን ውብ ጽዱ እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የሚከናወነው ተግባር በፍጥነት እየተፈጸመ ነዋሪውም ውጤቱን በተጨባጭ እየተመለከተ ይገኛል።
ይህ የሆነው ደግሞ በከተማዋ በተለወጠው 24/7 የመስራት የስራ ባህል እና ያልተቋረጠ የአመራር ክትትል ስራው በፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑ ነው።
በካዛንችስ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የህጻናት አለም ፓርክ ፣ በቦሌ መድኃኔዓለም እና 22 አካባቢ የሚገነቡ የኮሪደር ልማት አገናኝ መስመሮችን የምሽት የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የጎበኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማዋን የማልማቱ ተግባር የነገ ትውልድንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚካሄድ በመሆኑ የህጻናት አለም ፓርክ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
የፓርኩ ግንባታ ስራ በኢትዮጵያውያን ትጋት 24/7 እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ለግንባታው የሚውለው አብዛኛው ግብዓትም የሀገር ውስጥ መሆኑንና ለበርካቶችም የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በቦሌ መድኃኔዓለም እና በ22 አካባቢ የሚገነቡ የኮሪደር ልማት አገናኝ መስመሮች ግንባታም በተለመደው የግንባታ ፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን የሚናገሩት ከንቲባዋ የግል ዘርፉም በተለወጠው የስራ ባህል ለልማቱ አጋዥ እየሆነ ነው ብለዋል።
ይህ የከተማዋ የተለወጠ 24/7 የመስራት የስራ ባህል የከተማዋን ኢኮኖሚ 24 ሰዓት እያንቀሳቀሰ እና በርካታ የስራ እድሎችንም እየፈጠረ መሆኑን ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተናገሩት።
አዲስ አበባ ከተማን ለኑሮ ምቹ እና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብሎም መጪው ትውልድ ያደገች እና የበለጸገች ሆና የሚረካባት ለማድረግ የሚከናወነው ይህ ተግባር በተያዘው አግባብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የገለጹት።