በምስራቅ አፍሪካ የባህር ጠረፍ የኢትዮጵያ ተጠቃሚ አለመሆን ፍትሕዊነት የጎደለው ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ የባህር ጠረፍ የኢትዮጵያ ተጠቃሚ አለመሆን ፍትሕዊነት የጎደለው ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፡- በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የባህር ጠረፍ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አለመሆኗ ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ስድስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተመለከቱ ጉዳዮችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የመሆን ጥያቄዋ የጋራ ብልፅግና መርህን የተከተለ ነው ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ከምፅዋ እስከ ሞቃዲሾ ያለው የቀይ ባህር ቀጣና አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የባህር ጠረፍ እንደሚሸፍን ገልጸው በዚህ ለሁሉም በሚበቃ ሰፊ የባህር ዳርቻ ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ተጠቃሚ አለመሆኗ ፍትሕዊነት የጎደለው ነው ብለዋል።
ይህ ጥያቄ ፍትዊ ካልሆነ ዓለም ላይ ፍትሕ የለም ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ካላገኘች ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር የኢኮኖሚ ዕዳ እንደምትሆን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን በኃይል ሳይሆን በሰላማዊ መንገድና በሕግ አግባብ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሊዝ ስምምነት የወደብ አገልግሎት ባለቤት መሆን እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ትልቅ የገበያና የኢኮኖሚ አቅም በመሆኗ ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ተደጋግፈው ማደግ እንጂ ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ፀጋዋ በማራቅ ትርፋማ መሆን እንደማይችሉ ገልጸዋል።