ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመቻቸው ሀገራዊ የምክክር ዕድል በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በሰጡት ማብራሪያ፤ ምክክር ልብን ያሳርፋል፤ ውይይትም ስብራትን ይጠግናል ሲሉ የምክክርን ፋይዳ አስረድተዋል።

የአሁኑ ትውልድም ቅድመ አያቶች ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት የከፈሉትን የጀግንነት ወኔ በመላበስ፣ በሰለጠነ የምክክር አውድ የተሰራች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ እስካሁን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ማወያየቱን ጠቅሰው፤ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ እና በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በርካታ አጀንዳዎችን መሰብሰቡን ገልጸው፣ እስካሁን የአጀንዳ ማሰባሰብና ለዋናው መድረክ የሚወያዩ ሰዎችን የመለየት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን መፍጠሪያ መሳሪያ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመቻቸው ሀገራዊ የምክክር ዕድልም በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምክክር ሂደቱ ባለድርሻ አካል በመሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጀንዳዎች በአግባቡ በማሰባሰብ ለምክክር ኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

የክልል ፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቶችም በሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አጀንዳዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ወቅት ከምክክር ሂደቱ ወጥተው የነበሩ የተወሰኑ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በማድረግ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መደረጉን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመገንባት ለቀጣዩ ትውልድ ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ሀገር ለማስተላለፍ ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጋራ ምክር ቤቱ የሚያቀርቡት ሃሳብና አስተያየትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በተሻለ ምዕራፍ እየተጓዘ መሆኑን እንደሚያስረዳም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የቅራኔ መፍቻ ቁልፍ መሳሪያ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ከሰለጠነ የምክክር አውድ ውጭ የሚደረጉ አካሄዶች በኢትዮጵያ ላይ ጥፋትን ከማስከተል ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም በዜጎች መካከል የተፈጠሩ ቅራኔዎችን መፍትሔ ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ እኩል የሚሳተፍበትን ዕድል እንደከፈተ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም