ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ትሳተፋለች

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው 39ኛውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ጣሊያን ፎረምን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

39ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ቀደም ብሎ ደግሞ 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡


 

የዘንድሮው ጉባኤ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በመል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ ጉባኤው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዝግጅቷን አጠናቃለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረተጓንም ገልጸዋል፡፡

"ሁሉም ለሀገሩ ዲፕሎማት ነው" በሚል መርህ 179 በጎ ፈቃድ ሰጪዎች አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ጉባኤውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የተለያዩ ተቋማት ቀልጣፋና እንግዶችን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዘንድሮው መሪ ቃል ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች ማከናወኗን ገልጸው፤ በጉባኤው በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶችና ተሞክሮዎቿን ታካፍላለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመሪዎቿ እና በሚኒስትሮቿ አማካኝነት በርካታ ውይይቶችን ለማድረግ መዘጋጀቷንም ጨምረው አመላክተዋል።

የአፍሪካ ጣልያን የመሪዎች ስብሰባ የካቲት 6 እንደሚካሄድም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

በዚህም ከአስተናጋጅነት ባለፈ ብሔራዊ ጥቅሞቿን የሚያስጠብቁ ስራዎችን እንደምትሰራ ተናግረዋል።

39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ጣሊያን ስብሰባ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግም አምባሳደር ነብያት ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም