ቀጥታ፡

የጤና ተቋማትን በሰው ኃይልና በግብዓት በማጠናከር የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

ነቀምቴ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፡- የጤና ተቋማቱን በሰው ኃይልና በግብዓት በማጠናከር  የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጤና ሚኒስትር የተመራ ቡድን በነቀምቴ ከተማ የሚገኙ የወለጋ ዩኒቨርስቲ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታልን፣ የነቀምቴ ከተማ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን፣ ሪጅናል ላብራቶሪን፣ የመድኃኒት ፈንድ  እና ሌሎች የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በወቅቱ እንዳሉት፤ የጤና አገልግሎት ደረጃን  በማሻሻልና ጥራቱን በማስጠበቅ ጤናማ ማህበረሰብን  ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል። 


 

ለዚህም የጤና ተቋማቱን በግብዓት አቅርቦትና  በሰው ኃይል ልማት ለሟሟላት  እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለተግባራዊነቱም የጤና ተቋማቱን አቅም ለመለየት በየጊዜው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አንስተው በምስራቅ ወለጋ ዞን የተደረጉ ጉብኝቶችም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ተቋማቱን አቅም በማጠናከር የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግም የመድኃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በወቅቱም ሚኒስቴሩ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የሕክምና መገልገያ ግብዓቶችን ለምስራቅ ወለጋ ዞንና ነቀምቴ ከተማ ጤና ተቋማት ድጋፍ  ማድረጉን አንስተዋል።  

በነቀምቴ ከተማ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቨ ሆስፒታል አራት የኩላሊት እጥበት ማሽኖችን አስገብቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም የካንሰር ኬሞ መስጠት መጀመሩ በተለይ ለምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል ትልቅ እፎይታ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና የታካሚው ቁጥር እና ያለው አቅርቦት አለመመጣጠን መኖሩን ማስተዋላቸው እና ይህንን ለመቅረፍ እንደሚሰራም  ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ፕሮፌሰር ነፃነት ወርቅነህ በበኩላቸው በጤና ሚኒስትር የተመራ ቡድን በነቀምቴ ከተማ ተገኝቶ  የተከናወኑ ተግባራትን በመጎብኘት ድጋፍ ማድረጉ የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።

የጤና ሚኒስቴር ያደረገው ድጋፍም ለማህበረሰቡ ጥራት ያለው  አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸው የተደረጉ የመድኃኒትና የቁሳቁስ ድጋፎችም ያለውን እጥረት ሙሉ በሙሉ ባይቀርፉም እንደሚያቃልሉ ገልጸዋል።

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የጤና አገልግሎት አሰጣጡን በአካል ተገኝቶ በመገምገም የስራ አቅጣጫ መስጠታቸው  ለችግሮች በጋራ መፍትሄው ለመስጠት ያግዛል ያሉት ደግሞ የምስራቅ ወለጋ ዞን ጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቡልቶሳ ቡሻ ናቸው።

በጤና ሚኒስቴር እና በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ለተደረገው የመድኃኒትና የቁሳቁስ ድጋፍም አመስግነዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም