የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ላይ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ላይ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ይጠበቃል
አሶሳ፤ ጥር 28/2018(አዜአ)፦ የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ላይ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ገለጸ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ንቅናቄ በአሶሳ ከተማ መናኸሪያ ዛሬ ማለዳ ላይ አስጀምሯል።
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ፤ በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ እንደተናገሩት የትራፊክ አደጋ በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ለአሽከርካሪዎች፣ ለህብረተሰቡ እና ለሌሎች አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ንቅናቄው ህብረተሰቡ የትራፊክ ደህንነት ህጎችን በአግባቡ እንዲገነዘብ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ለአሽከርካሪዎች ደግሞ የተሽከርካሪ ደህንነትን በመጠበቅ እና የትራፊክ ህጎችን በማክበር ከአደጋ ነፃ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል።
አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የትራፊክ አደጋ መከላከል የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዙሪያ ዜጎች የጠራ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አወቀ አይሸሹም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ በሁሉም ዘርፍ እየተመዘገበ ለሚገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት የትራንስፖርት ዘርፉ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ቢሮው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እያከናወነ ከሚገኘው የዕለት ተዕለት የቁጥጥር ስራ ጎን ለጎን የህብረተሰቡን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ንቅናቄውን እስከ ታች በማውረድ በክልሉ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ የክትትል እና ቁጥጥር ስራዎች በአሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
የትራፊክ አስተባባሪዎች እና አሽከርካሪዎች በበኩላቸው፤ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ለማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የትራፊክ አስተባባሪዎች፣ አሽከርካሪዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።